ትግራይ፡ በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ ሊመቻች መሆኑ ተገለፀ

  • ትግራይ፡ በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ ሊመቻች መሆኑ ተገለፀ - BBC News አማርኛ
  • 95

ትግራይ፡ በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ ሊመቻች መሆኑ ተገለፀ

የተፈናቀሉ ስደተኛ

የኢትዮጵያ መንግሥት የሠላም ሚኒስቴር የሚከታተለው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መተላለፊያ ሊያመቻች መሆኑ ተገለጸ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸውን ዜጎች እገዛ እያደረገም መሆኑን አስታውቋል።

ምግብ፣ መድኃኒት፣ ውሃና አስፈላጊ የሚባሉ መሰረታዊ የእርዳታ አቅርቦቶችንም የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች እየቀረበ መሆኑንም ጠቅሷል።

ከዚህም በተጨማሪ ሦስት ሳምንታትን ያስቆተረውን ግጭት ፈርተው ወደ ሱዳን ለሸሹት ሰዎች መጠለያ ካምፖች እንደሚያቋቁም መግለጫው አስፍሯል።

መንግሥት ጨምሮም በግጭቱ ሳቢያ ተፈናቅለው ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን ዜጎች ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ሂደት ውስጥም የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅና ለመደገፍ ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

በኢትዮጵያ፣ ትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ሸሽተው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡን ተከትሎ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች በፌደራል መንግሥት የእርዳታ መስመር እንዲመቻች በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን፤ ዩኤንኤችሲአር ከቀናት በፊት አስታውቋል።

የሰብዓዊ መብት እና እርዳታ ድርጅቶች ግጭቱ በቶሎ የማይቋጭ ከሆነ ከዚህ በበለጠ የሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በማለት ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።

ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብም ያስችል ዘንድ መተላለፊያ እንደሚያመቻችም ተጠቅሷል።

ባለስልጣናቱ ከተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችም ሆነ ድርጅቶች ጋር ለመስራትም ቁርጠኝነት እንዳለው መግለጫው አስፍሯል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችና የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች እንዳሳሰበውም ዩኤንኤችሲአር ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ዩኤንኤችሲአርም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት አጋሮች ሁለቱም ወገኖች የዓለም አቀፍ ሕግን አክብረው ንፁሃን ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ነፃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀና እክል በሌለበት ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻችም ጠይቋል።

በኢትዮጵያ፣ በትግራይ ክልል ያሉ 100 ሺህ ኤርትራውያን ተፈናቃዮችም በግጭቱ ምክንያት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

ምግብ፣ ውሃ፣ መድኃኒትን የመሳሰሉ መሰረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶችን ማድረስ አስቸጋሪ በመሆኑም ለስደተኞቹ ያለው ክምችትም በሳምንት ውስጥ ሊያልቅ መቻሉ ከፍተኛ ስጋት ሆኖብኛል ብሏል ድርጅቱ።

ሁለቱም አካላት ነፃና ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ ዜጎች እርዳታ ወደሚያገኙበት ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸውን እንዲያከብሩ ዩኤንኤችሲአር ጠይቋል።

ድርጅቱ አክሎም ተፈናቃዮች በብሔር ልዩነት ሳይደረግባቸው ደኅንነት ወደሚሰማቸው ቦታ አንዲንቀሳቀሱ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ድንበሮችን እንዲያቋርጡም ሁለቱም ወገኖች ማመቻቸት አለባቸው ብሏል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች