ስፖርት፡ እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥቁር ስፖርተኛ ሐውልት ያቆመችው መቼ እንደሆነ ያውቃሉ?

  • 55

ስፖርት፡ እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥቁር ስፖርተኛ ሐውልት ያቆመችው መቼ እንደሆነ ያውቃሉ?

የቲየሪ ሄንሪ ሃውልት

ጃክ ሌዝሊ፤ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን ማልያ አጥልቆ ታሪክ ከሠራ 100 ዓመታት ሊሞላው ቢሆን እንኳ በቅጡ የሚያስታውሰው ሰው አልነበረም። ይህ የሆነው በቆዳው ቀለም ብቻ ነው።

ጊዜው 1925 ነበር። እንግሊዝ ከአየርላንድ ጋር ለነበራት የወዳጅነት ጨዋታ መልማዮች ተጫወቾችን እየመለመሉ ነበር። በወቅቱ ሌዝሊ የፕላይማውዝ ተጫዋች ነበር።

መልማዮቹ የሚጫወትበት ሜዳ መጥተው ሲመለከቱ ሌዝሊን ጥቁር ሆኖ ያገኙታል። በዚህም ምክንያት ሌዝሊ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የተሰለፈ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን ታሪክ የሚሠራበትን አጋጣሚ መና ያደርጉበታል።

ይኸው ሌዝሊ አሁን ገንዘብ ተዋጥቶለት ሃውልት ሊሰራለት እየታቀደ ነው። እስካሁን ቢያንስ 135 ሺህ ፓውንድ ተዋጥቶለታል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ 240 ስፖርተኞችን የሚዘክሩ ሃውልቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል 10 ብቻ ናቸው ለጥቁርና አናሳ ቁጥር ላላቸው እንግሊዛውያን ክብር የቆሙት።

ከአስሩ መካከል አምስት ለእግርኳስ ተጫዋቾች የቆሙ ሲሆን ጎልፍና ክሪኬት የመሳሰሉ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ምንም ዓይነት የጥቁር ግለሰብ ሐውልት የላቸውም።

ለምን?

ሼፊልድ ዩኒቨርሲቲ የሠራው አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው የጥቁር ስፖርተኞች ሐውልቶች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ባለፉት 10 ዓመታት ነው።

አብዛኛዎቹ ሐውልቶች በተለይ ደግሞ የእግር ኳስ ተጫዎቾች መታሰቢያዎች ተጫዎቾቹ ጫማ ከሰቀሉ ከ20ና 30 ዓመታት በኋላ ነው የሚሠሩት።

አብዛኛዎቹ የጥቁር እግር ኳስ ተጫዋቾች ሐውልቶች ለምን ባለፉት 10 ዓመታት ተሰሩ የሚለውን ጥያቄ የሚመልሱት ዶ/ር ክሪስ ስትራይድ፤ በእንግሊዝ እግር ኳስ መድረክ ከ1980ዎቹ [በአውሮፓውያኑ] በፊት በጣም ጥቂት ተጫዋቾች ነበሩ ይላሉ።

ዩናይትድ ኪንግደም ካላት 240 ሐውልት መካከል 10 ሃውልቶች ለጥቁሮች መድባለች። ከእነዚህ መካከል ዘጠኙ የተገነቡት ባለፉት 10 ዓመታት ነው። ይህ ደግሞ የ1980ዎቹ ተጫዎቾች መታሰብ የጀመሩት አሁን መሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ ምሁሩ።

እንግሊዝ ውስጥ ከቆሙ የጥቁር ተጫዋቾች ሐውልቶች መካከል ጎልቶ የሚወጣው በአውሮፓውያኑ 2019 የተገነባው የሶስቱ የዌስት ብሮሚች አልቢዮን ተጫዎቾች ሃውልት ነው።

ሎሪ ካኒንግሃም፣ ሲሪል ሬጂስና ብንዶን ባስቶን ዌስትብሮም በ1970ዎቹ በእንግሊዝ እግር ኳስ ታዋቂው ቡድን እንዲሆን የጎላ ሚና ተጫውተዋል።

እንግሊዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ለጥቁር ስፖርተኛ ሃውልት ያቆመችው በአውሮፓውያኑ 2001 ነው። ይሄም የታዋቂው ቦክሰኛ ራንዲ ቱርፒን ነው። ከዚያ በመቀጠል ሐውልት የቆመለት ጥቁር ተጫዋች የአርሰናሉ ፈረንሳዊ አጥቂ ቲየሪ ሄንሪ ነው።

ሴቶች?

ዩናይትድ ኪንግደም በዓለማችን በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሃውልቶች ያሏት ሃገር ናት። በጠቅላላው በዓለማችን 700 የእግር ኳስ ተጫዋቾች ሐውልት እንደቆመላቸው አንድ ጥናት ይጠቁማል።

ነገር ግን ከእነዚህ ሐውልቶች መካከል ለሴት ስፖርተኞች መታሰቢያ የሆኑ ዘንድ የቆሙ ሐውልቶች በጣም ጥቂት ናቸው።

ሊሊ ፓር እንግሊዝ ውስጥ ሐውልት የተሰራላት የመጀመሪያዋ ሴት ስፖርተኛ ናት። በ1920ዎቹና 30ዎቹ ዲክ ለተሰኘው የሴቶች እግር ኳስ ቡድን የተጫወተችው ሊሊ ሃማንቸስተር ውስጥ ሐውልት የተሰራላት ባለፈው ዓመት [2019] ነው።

ከሊሊ በተጨማሪ ሃውልት የቆመላቸው እንግሊዛውያን ስፖርተኞች 3 ናቸው። እነዚህም ቴኒስ ተጫዋቿ ዶሮቲ ራውንድ፣ የኦሊምፒክ ሻምፒዮናዎቹ ሜሪ ፒተርስና ኬሊ ሆልምስ ናቸው።

ከ1980ዎቹ በኋላ ያለው የእንግሊዝ እግር ኳስ በጥቁር ተጫዎቾች የደመቀ ነው። ያለፈው አስር ዓመትም ጥቁር የእግር ኳስ ፈርጦችን አፍርቷል። የእነዚህን ተጫዎቾች ሐውልት መች እናይ ይሆን? የበርካቶች ጥያዌ ነው።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች