ኮሮናቫይረስ፡ ኦሃዮ ይከተቡ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያሸንፉ እያለች ነው

 • ኮሮናቫይረስ፡ ኦሃዮ ይከተቡ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያሸንፉ እያለች ነው - BBC News አማርኛ

  ኮሮናቫይረስ፡ ኦሃዮ ይከተቡ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያሸንፉ እያለች ነው

  ሳሚ ቤትስ ክትባት እየተከተበች

  የፎቶው ባለመብት, Reuters

  የዩናይትድ ስቴትሷ ኦሃዮ ግዛት የኮቪድ-19 ክትባት ለወሰዱ አምስት ሰዎች አንድ ሚሊዮን ዶላር በዕጣ በመሸለም ብዙ ሰዎች እንዲከተቡ እያበረታታች ነው።

  የኦሃዮ አስተዳዳሪ ማይክ ዲዌይን ለዕጣው ዕጩነት ብቁ የሚሆኑት የተከተቡ ጎልማሳ ነዋሪዎች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

  ከአምስቱ ሳምንታዊ ዕጣዎች የመጀመሪያው ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡

  ለባለዕድለኞች የሚከፈለው ገንዘብ ከፌደራል መንግስት ለኮሮናቫይረስ ከሚሰጥ ፈንድ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

  አሜሪካ 58.7 በመቶ ጎልማሳ ዜጎቿን በመከተብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ሆናለች፡፡

  ከ 32 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውባት ከዓለም ቀዳሚ የሆነችው ሃገሪቱ ወረርሽኙን ለመግታት የተሳካ የክትባት ፕሮግራም ያስልጋታል ተብሏል፡፡

  የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአሜሪካ የነጻነት ቀን እስከሚከበርበት ሐምሌ 4 ቀን ድረስ 70 በመቶ አዋቂዎችን የመከተብ ግብ አስቀምጧል፡፡

  ሆኖም በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ክትባት ለሳምንታት እየቀነሰ ሄዷል፡፡ የጤና ባለሥልጣናት ጉዳዩን ከአንዳንድ አሜሪካውያን ማመንታት ጋር አቆራኝተውታል፡፡

  ያመነቱትን ለማሳመን ቢራ፣ ዶናት፣ የስፖርት ውድድሮች ትኬት እና የገንዘብ ሽልማቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሳቢ ስጦታዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተሰጡ ይገኛል፡፡

  ዲዌይን የኦሃዮን ሎተሪ በትዊተር ይፋ ሲያደርጉ "አንዳንዶች 'ዲዌይን ፣ እብድ ነህ? ይህ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ ሃሳብ ገንዘብ ማባከን ነው' ሊሉ እንደሚችሉ አውቃለሁ። እውነታው ግን በወረርሽኙ ወቅት ያለው ትክክለኛ ብክነት ክትባቱ ለሚፈልገው ሁሉ በቀላሉ እየተገኘ በኮቪድ -19 የሚጠፋው ሕይወት ነው" ብለዋል።

  ግዛቲቱ ዕድሜያቸው ከ 18 ዓመት በታች ለሆኑና ለክትባት ነዋሪዎችም ሎተሪ አዘጋጅታለች።

  እነዚህኞቹ ከአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ሎተሪ ውጭ ቢሆኑም ከኦሃዮ ግዛት ዩኒቨርሲቲዎች በአንዱ ሙሉ የአራት ዓመት ነጻ የትምህርት ዕድል በሚያስገኘው ዕጣ ይካተታሉ፡በሎተሪው የሚተካተቱ ሰዎች የስም ዝርዝር ከክልሉ የመራጮች ምዝገባ የመረጃ ቋት እንደሚወሰድ ዲዌይን ተናግረዋል፡፡

  ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ባይደን የክትባቱን "ተጠራጣሪዎች" ለማሸነፍ አስተዳደራቸው እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረትም የ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ልጆች ክትባት ተካቷል፡፡

  የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ሰኞ ዕለት ከ 12 እስከ 15 ዓመት ለሆኑ ታዳጊ ወጣቶች የፋይዘር /ባዮኤንቴክ ክትባት አንዲሰጣቸው አጽድቋል።

  የአስተዳደሩ ኮሚሽነር ዶ/ር ጃኔት ውድኩክ እርምጃው ወደ "መደበኛ ህይወት እንድንመለስ እና የተከሰተውን ወረርሽኝ ለማቃለል" ያለመ ነው ብለዋል፡፡  • ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች