መዝናኛ፡ የኤምቲቪ (MTV) ባለቤት ሞቱ

  • 50

መዝናኛ፡ የኤምቲቪ (MTV) ባለቤት ሞቱ

ሰምነር ሬድስቶን

"የአሜሪካ ሚዲያና መዝናኛ አባት" የሚባሉት ሰምነር ሬድስቶን በተወለዱ በ97 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ሬድስቶን ከአባታቸው የተረከቡትን ናሽናል አሚይዝመነት የተሰኘውን የመካነ መኪና ሲኒማ (drive-in Cinema) ሥራን ወደ ቢሊዮን ዶላር ቢዝነስ መቀየር የቻሉ ብርቱ ሰው ነበሩ፡፡

"ድራይቭ ኢን ሲኒማ" ሰዎች ከመኪናቸው ምቾት ሳይለዩ በሕዝብ አደባባዮችና ሌሎች ገላጣ ቦታዎች ሲኒማ የሚመለከቱበት አማራጭ ነው፡፡

አቶ ሬድስቶን አሁን እጀግ ዝነኛ የሆኑትን ፊልም አምራቾችና አቅራቢዎች፣ የዜናና የመዝናኛ ተሌቭዥኖችን ለመቆጣጠር የቻሉ ጎምቱ የመዝናኛ ኢንዱስትሪው ሰው ናቸው፡፡

ከሕልፈታቸው በፊት ግዙፎቹን ቫያኮም ኮርፖሬሽንን፣ ፓራማውንት ፒክቸርስ (Paramount Pictures )፣ ሲቢኤስ (CBS) ኮርፖሬሽን እና ኤምቲቪ (MTV) ን በእጃቸው ማስገባት ችለዋል፡፡

ሰውየው በባሕሪያቸው ፍርሃት ያልፈጠረባቸውና በሥራ ጉዳይ ከትልልቅ ኃላፊዎች ጭምር የሚጋጩ ትጉህ ሰው ነበሩ፡፡ ከቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር ሲጨቃጨቁ እንደኖሩና ኃያል ሰው መሆናቸውን የሥራ ታሪካቸው ያወሳል፡፡

የመልቲፕሌክስ ፈጣሪ

ሬድስቶን በ1960ዎቹ ሲኒማን ወደ ገበያ ማዕከላት (ሞል) ውስጥ በማስገባት የመልቲፕሌክስ ሐሳብን በማምጣት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገርለቸዋል፡፡

በመልቲፕሌክስ በአንድ ጥላ ሥር ከአንድ በላይ ሲኒማ ቤቶች ኖረው አገልግሎት የሚሰጥበት ስልት ነው፡፡

የሬድስቶን ኩባንያ በመጨረሻ በዓለም ላይ ዋና ዋና የሲኒማ፣ ቴሌቪዥንና ኅትመት ሥራን በመጠቅለል ስመ ገናና ነው፡፡

የኒኬሎዲያን ቲቪ ባለቤት

ሬድስቶን ከኤምቲቪ በተጨማሪ በመላው ዓለም በተለይ የልጆች መዝናኛዎችን በማቅረብ የሚታወቀውን ኒኬሎዲያ ቲቪ መዝናኛን፣ ከበርካታ ሌሎች የቲቪ ኔትወርኮች አዳብለው በባሌበትነት ይዘውታል፡፡

ከዚህም በላይ መቀመጫውን ማንሐተን ያደረገውን ዝነኛውን ኮሜዲ ሴንትረም ኬብል ቻናልን የአንበሳ ድርሻ የያዙት ሬድስቶን ነበሩ፡፡ ኮሜዲ ሴንትረም እውቅ የቲቪ መርሀግብቶችን የሚያሰናዳ ሲሆን እስከ 100 ሚሊዮን አባወራዎች/እማወራዎች ዘንድ ይደርሳል፡፡

በርሳቸው አጋፋሪነት ለሕዝብ ከደረሱ የሲኒማ ውጤቶች አንዱ ተወዳጁ ‹‹ዘ ቢግ ባንግ ቲዎሪ›› ተከታታይ ፊልም ይገኝበታል፡፡

ታይታኒክ እና ቶፕ ገን ፊልሞችም ላይ የርሳቸው ድርሻ የሚናቅ አልነበረም፡፡

ሴት ልጃቸው ሻሪ ሬድስቶን አባቴ የኖረው ሕይወት ላቅ ያለ ነበር ብላለች፡፡ ‹‹የአሜሪካንን የመዝናኛ ዘርፍ አሁን ባለበት ቅርጽ ያደረሰው አባቴ ነው ብላለች፡፡››

አክላም፣ ‹ሬድስቶን ተወዳጅ አባት፣ አያትና ቅድመ አያት የሆነ ሰው ነው፤ ነፍስ ይማር ብላለች፡፡››

ሰውየው እጅ የማይሰጡ መሆናቸውን ያስመሰከሩት የቪየኮምና እና የሲቢኤስ የቦርድ ሊቀመንበርነታቸው ያስረከቡት በ92 ዓመታቸው በ2016 እንደ አውሮጳዊያኑ መሆኑ ነው፡፡

ሮድስቶር በ2009 በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ ‹‹ ለጊዜው ጡረታ የመውጣትም ሆነ የመሞት እቅድ የለኝም ብለው ቀልደው ነበር፡፡

ፎርብስ የአዱኛ አጋላጭ መጽሔት የሰውየውን ሀብት ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ያስጠጋዋል፡፡• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች