አማራ ክልል፡ በደሴ ማረሚያ ቤት 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

  • 70

አማራ ክልል፡ በደሴ ማረሚያ ቤት 13 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ

ደሴ ከተማ

በደሴ ማረሚያ ቤት በተደረገ የኮቪድ-19 ምርመራ 13 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ማረጋገጡን የከተማው ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አብዱልሃሚድ ይመር በተለይ ለቢቢሲ እንዳስታወቁት 12ቱ የህግ ታራሚዎች ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ የማረሚያ ቤቱ ባልደረባ ናቸው።

እንደ አቶ አብዱልሃሚድ ገለጻ ከሆነ ከማረሚያ ቤቱ ጋር በመነጋገርም አዲስ የሚገቡ ታራሚዎች ለ14 ቀናት ለብቻቸው እንዲቆዩ ከማድረግ በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ምርመራ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

ከሐምሌ 20 በኋላ ማረሚያ ቤቱ የገቡ 46 ታራሚዎች ላይ በተደረገ ምርመራ 10 ሰዎች ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ለማረጋገጥ ተችሏል።

“ታራሚዎቹ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ናቸው። ከተለያዩ ከደቡብ ወሎ ወረዳዎች እና ከደሴ ከተማም የተገኙ ናቸው” ብለዋል።

በሁለተኛ ዙር 60 ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ ሦስቱ ቫይረሱ እንዳለባቸው ተረጋግጧል።

በሁለተኛው ዙር ቫይረሱ ከተገኘባቸው መካከል በመጀመሪያው ዙር እንዳለባቸው ከታወቁ ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው እና አንድ ማረሚያ ቤቱ ባልደረባ ይገኙበታል።

የማረሚያ ቤቱን የሕግ ታራሚዎች እና ባልደረባዎችን በሙሉ ለመመርመር መቻሉንም አቶ አብዱልሃሚድ አስታውቀዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ቦሩ ሜዳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የተላኩ ሲሆን፤ ተጓዳኝ ህመም ያለበት አንድ ታራሚ ካሳየው የህመም ምልክት ውጭ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በማረሚያ ቤቱ የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋ አዲስ የሚገቡትን እና ነባር ታራሚዎችን ከመመርመር ባለፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ የኬሚካል ርጭት፣ ርቀትን ማስጠበቅ እና ንጽህና የማስጠበቅ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ባለፉት ወራት በአማራ ክልል በተደረገ የኮሮናቫይረስ ምርመራ 83 አሽከርካሪዎች እና ረዳቶቻቸው ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

በክልሉ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካካል 23 የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገኙበትም ከአማራ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25,118 የደረሱ ሲሆን የሟቾች ቁጥር 463 ደርሷል። እንዲሁም አጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች 11,034 ደርሰዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች