ኮሮናቫይረስ፡ ስለወረርሽኙ ሊያውቋቸው የሚገቡ ወሳኝ ነጥቦች

  • 18 ማርች 2020
  • 282
ጭንብል ያደረገች ሴትImage copyright EPA

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት መካከል ከ150 በላይ በሚሆኑት ውስጥ መከሰቱ ተረጋግጧል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ሰዎች ስለበሽታው ለማወቅ የተለያዩ ጥያቄዎችን እየጠየቁ ነው።

እኛም ታዳሚዎቻችንን በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ማወቅ ስለሚፈልጓቸው ነገሮች ጠይቀናቸው የብዙዎች ጥያቄ የሆኑትን መርጠን አቅርበናል።

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ቫይረሱን ለመካላከል ይጠቅማል?

በሽታውን በመከላከል በኩል የፊት ጭንብል የሚኖረውን አስተዋጽኦን በተመለከተ በጣም ውስን መረጃ ብቻ ነው ያለው።

ሕንድ በስልክ ጥሪ ስለኮሮናቫይረስ መረጃ እየሰጠች ነው

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ወረርሽኙን ለመከላከል የግል ንጽህናን በአግባቡ መጠበቅ ወሳኝ ነው። በተለይ ደግሞ እጃችንን ወደ አፋችን፣ አፍንጫችንና ዓይናችን ከማስጠጋታችን በፊት በአግባቡ መታጠብ ከሁሉ የላቀ ውጤታማ መከላከያ ነው።

ቫይረሱ በበር እጀታዎች አማካይነት ሊተላለፍ ይችላል፤ ለምን ያህልስ ጊዜ በእጀታዎች ላይ ሊቆይ ይችላል?

ቫይረሱ ያለበት ሰው እጁ ላይ አስሎ ወይም አስነጥሶ የበር እጀታዎችንና ሌሎች ነገሮችን ከነካ ቫይረሱን ወደ ተነካው እቃ ሊያሸጋግር ይችላል።

የበር እጀታዎች በተለያዩ ሰዎች ስለሚነኩ በሽታውን በማስተላለፍ በኩል አንድ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ በተለያዩ ቁሶች ላይ ለቀናት በህይወት በመቆየት ወደ ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል።

ኮሮናቫይረስና የአእምሮ ጤና ምን አገናኛቸው?

ስለዚህም በበሽታው ላለመያዝና ስርጭቱን ለመግታት እጅን በመደበኛነት መታጠብ ወሳኙ የመከላከያ መንገድ ነው።

የኮሮናቫይረስ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፋል?

በሽታው በግብረ ሥጋ ግንኙነት ይተላለፍ እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በአሁኑ ወቅት ለበሽታው መተላላፊያ ተብለው የሚጠቀሱት ማሳል፣ ማስነጠስና በቫይረሱ የተበከሉ ነገሮችን መንካት ናቸው።

የኮሮናቫይረስ ህመም ምልክቶች

በጉንፋንና በኮሮናቫይረስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

የኮሮናቫይረስና ጉንፋን የሚጋሯቸው ተመሳሳይ የበሽታ ምልክቶች ስላሏቸው ለመለየትና ለመመርመር አስቸጋሪ ሆኗል።

የኮሮናቫይረስን ለመለየት በዋናነት ማተኮር ያለብን ምልክቶች ትኩሳትና ጠንካራ ሳል ናቸው።

ጉንፋን ግን የጉሮሮ ህመምን ጨምሮ ሌሎች ምልክቶችን የሚያሳይ ሲሆን ኮሮናቫይረስ ደግሞ የትንፋሽ ማጠር ያስከትላል።

የኮሮናቫይረስ ከጉንፋን የበለጠ ተላላፊ ነው?

በጉንፍንና በኮሮናቫይረስ መካከል ቀጥተኛ ንጽጽር ለማድረግ ጊዜው ገና ቢሆንም ነገር ግን ሁለቱም ቫይረሶች በከፍተኛ ደረጃ የሚተላለፉ ናቸው።

ተመራማሪዎች ሰውነታችን የኮሮናቫይረስን የሚከላከልበትን መንገድ መለየት ቻሉ

በኮሮናቫይረስ የተያዘ አንድ ሰው በአማካይ ከሁለት እስከ ሦስት ወደ የሚደርሱ ሰዎች የሚያስተላልፉ ሲሆን፤ ጉንፋን የያዘው ሰው ግን በሽታውን ወደ አንድ ሊያጋባ ይችላል።

ሁለቱም በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ሊተላለፉ ይችላሉ።

የኮሮናቫይረስ በሽታው ያለበት ሰው ባዘጋጀው ምግብ በኩል ሊተላለፍ ይችላል?

የኮሮናቫይረስ በሽታ ያለበት ሰው ምግቡን በሚያዘጋጅበት ወቅት ተገቢውን የንጽህና ጥንቃቄ ካላደረገ ወደ ተመጋቢው ሊተላለፍ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።

የኮሮናቫይረስ በሳልና በማስነጠስ በሚከሰቱ ብናኝ ጠብታዎች በእጅ አማካይነት ወደ ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል።

የቫይረሱ መስፋፋትን ለመግታት ምግብን ከመንካታችንና ከመመገባችን በፊት እጃችንን በደንብ አድርጎ መታጠብ ይመከራል።

የጽዳት ሥራ የሚያከናውኑ ሰዎች
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ በሽታውን ለመከላከል ወሳኝ ነው

በሽታው በተከሰተባቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው?

በሽታው መኖሩ በተረጋገጠባቸው አገራት የሚኖሩ ሰዎች በወረርሽኙ የመያዝ ዕድላቸውን ለመቀነስ መከተል ያለባቸው የተለያዩ እርምጃዎች አሉ።

ቫይረሱ በሳልና በማስነጠስ ጊዜ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ጠብታዎች በሰዎች መካከል በሚኖር ንክኪ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።

ስለዚህም የተለያዩ ሰዎች የሚነኳቸውን ነገሮችን ከመንካት መቆጠብ እንዲሁም አዘውትሮ እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ወይም ተህዋሲያንን በሚገድሉ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሾች [ሳኒታይዘር] እጅን ማጽዳት ያስፈልጋል።

በየደቂቃው በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን የሚያሳይ ካርታ

በተጨማሪም ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱና ትኩሳት ካለባቸው ሰዎች ጋር ቅርበትና ንክኪን ማስወገድ በቫይረሱ መያዝን ሊያስወግድ ይችላል።

በኮሮናቫይረስ ተይዣለሁ ተብሎ የሚታሰብ ከሆነም ከበሽታው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለመጠየቅ ወደ ተዘጋጁ የስልክ መስመሮች በመደወል ማሳወቅና ማድረግ ያለብንን መፈጸም ይኖርብናል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት አለ?

እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ እንዳንያዝ የሚያስችል ክትባት የሌለ ቢሆንም ተመራማሪዎች ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት ከፍተኛ ትረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የወረርሽኙ ቫይረስ ዝርያ ከዚህ በፊት በሰዎች ላይ ታይቶ የማይታወቅ አይነት በመሆኑ ሃኪሞችና ተመራማሪዎች ስለቫይረሱ በዝርዝር ለማወቅ ጊዜ ሳያስፈልጋቸው አይቀርም።

የአየር ሁኔታና ሙቀት በበሽታው መስፋፋት ላይ ተጽእኖ ይኖረው ይሆን?

በየወቅቱ የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለውጥ በበሽታው መስፋፋት ላይ የሚኖረውን ውጤት በተመለከተ አስካሁን ድረስ የታወቀ ነገር የለም።

ምንም እንኳን ጉንፋንን የመሳሰሉ አንዳንድ ቫይረሶች ወቅታዊ የአየር ሁኔታን እየተከተሉ የሚከሰቱና የሚስፋፉ ቢሆንም ከኮሮናቫይረስ አንጻር እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቤተሰብ በሆነው 'መርስ' ተብሎ በሚታወቀው ቫይረስ ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በሽታው ሞቃት በሆነ ጊዜ በስፋት የመከሰት ባህሪይ እንዳለው ተገልጿል።

ኮሮና


• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች