ትግራይ፡ ኤርትራ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ግጭት እጇን አስገብታለች?

  • ትግራይ፡ ኤርትራ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ግጭት እጇን አስገብታለች? - BBC News አማርኛ

ትግራይ፡ ኤርትራ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ግጭት እጇን አስገብታለች?

ሁመራ አካባቢ ያሉ ወታደሮች

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራል መንግሥትና የትግራይ ክልል ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ወደ ወታደራዊ ውጊያ ከተሸጋገረ ከሦስት ሳምንታት በላይ ሆኖታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የትግራይ ፀጥታ ኃይሎች በትግራይ የሚገኘውን ትልቁንና በትጥቅ የተደራጀውን የመከላከያ ሠሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልፀው ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት ከማምራቱ በፊት በፌደራል መንግሥትና የትግራይን ከልል በሚመራው ህወሓት መካከል የነበረው መቃቃር የተባባሰው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው በአገሪቱ ታቅዶ ነበረው ምርጫ እንዲራዘም የሰጡትን ውሳኔ ባለመቀበል የትግራይ ክልል የተናጠል ምርጫ ማድረጉን ተከትሎ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ "ኢ-ሕገ መንግሥታዊና ተቀባይነት የሌለው" ባለው በዚህ ምርጫ ህወሓት በማሸነፉ "ሕጋዊ አስተዳደር መስርቻለሁ" ብሏል።

ለሳምንታት በዘለቀው ግጭት የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ዋና የምትባለውን የሽሬን፣ አድዋን፣ አክሱምንና አዲግራትን ጨምሮ ምዕራባዊ ትግራይ ግዛቶችን ተቆጣጥሯል፤ እንዲሁም በደቡብ በኩልም ራያን በቁጥጥሩ ስር አድርጓል።

በግጭቱ የሞቱና የቆሰሉ አካላት እንዳሉ ከሁለቱም ወገን ቢጠቀስም ቁጥሩ አልተገለፀም።

ከዚህም በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ሸሽተው ወደ ሱዳን የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ዩኤንኤችሲአር ቁጥሩን ከ40 ሺህ በላይ መድረሱን አስታውቋል።

በትግራይ ክልል የሚደረገው የአየር ጥቃት መቀጠሉ ተገልጿል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጦርነቱ ውስንና በተወሰኑ የህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረና ሕገ መንግሥትን ለማስከበር እየተወሰደ ያለ እርምጃ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ መግለፃቸው ይታወሳል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት እንደተከፈተበትና ሕዝቡም ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል ያለው የውጊያው ሌላ ገፅታ ደግሞ የአገር ውስጥ ግጭት ቢሆንም ጎረቤት አገር ኤርትራ በግጭቱ ውስጥ እጇን አስገብታለች መባሏና ያላት ሚና ጥያቄ ሆኗል።

በግጭቱ ላይ የኤርትራ ሚና ምንድን ነው?

ኤርትራ ሠራዊቷን በድንበር በኩል በሽራሮ እንዲሁም በአላማጣ በኩል ከፌዴራል መከላከያ ሠራዊት ጋር እንዳሰለፈች የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የኤርትራ መንግሥት በቀጥታ ተሳታፊ መሆኑን ህዳር 1/2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ የኤርትራ ሠራዊት አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ከፍተኛ ድብደባ ፈፅመዋል ሲሉ ከሰዋል።

የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከፌደራል መንግሥት ጋር በመወገን በሁመራ በኩል በካባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት እንደፈፀሙና ድንበር ጥሰው በባድመ በኩል በመግባት ጦርነት ከፍተዋል ብለዋል በወቅቱ በሰጡት መግለጫ።

ይህንንም ተከትሎ ከትግራይ ክልል የተነሱ ተወንጫፊ ሮኬቶች በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ኢላማ አድርገዋል። አየር ማረፊያው የኤርትራ አየር ኃይልም የሚገኝበት ነው።

ከክልሉ የተነሱ ሦስት ሚሳይሎች ወደ ኤርትራ የተወነጨፉ ሲሆን አንደኛው አየር ማረፊያው አካባቢ ሲወድቅ ሁለቱ ደግሞ መኖሪያ ሰፈሮች መውደቃቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ኤርትራንና ኢትዮጵያን በሚያዋስነው ድንበር በኩል በተለያዩ ግንባሮች ከባድ የጦር መሳሪያዎች የተሳተፉበት ውጊያ መደረጉንም ቢቢሲ ከምንጮቹ ሰምቷል።

ግጭቶቹም በአሊቴና፣ ዛላምበሳ፣ ፆረናና መረብ በኩል መከሰቱም ሪፖርት ተደርጓል፤ እነዚህ ቦታዎች በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት(1990-1992) ወቅት የግጭቱ ገፈት ቀማሽ ነበሩ።

ኤርትራ ምላሽ ምንድን ነው?

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትን ክስ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ ህዳር 1/ 2013 ዓ.ም ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

"ይህ ውስጣዊ ግጭት ነው። እኛ የግጭቱ አካል አይደለንም" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በስልክ እንደገለጹለት ሮይተርስ ዘግቧል።

በለንደን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲም በበኩሉ የዩናይትድ ኪንግደም ኢንተር ፓርቲ የፓርላማ ቡድን የትግራይ ክልል ከኤርትራ አደጋ ተጋርጦበታል ብሎ የሰጠውን መግለጫ አጣጥሏል።

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ ሐብተማርያም ለኮመን ዌልዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ በፃፉት ደብዳቤ "የትግራይ ክልል ከኤርትራ መንግሥት በኩል አደጋ ተጋርጦበታል በሚል ያወጣውን የፓርላማ ቡድን ሪፖርት አይቀበልም" ብለዋል።

በፀረ-ህወሓት ትዊታቸው የሚታወቁት አምባሳደሩ አሥመራ ላይ የተወነጨፉትንም ሚሳይሎች በተመለከተ ምላሽ ሰጥተዋል።

"ህወሓት ሕገወጥ የሆነና የሃሞተ ቢስ ተግባር ህዳር 4/ 2013 አከናውኗል" ያሉት አምባሳደር እስጢፋኖስ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትንም በመጀመር ህወሓን ወንጅለዋል።

አምባሳደሩ ይህንን ይበሉ እንጂ ከ100 ሺህ ሰዎች በላይ በነጠቀውን ጦርነት የጀመረችው ኤርትራ መሆኗን የግልግል ዳኝነት ኮሚሽን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ምላሽ ውጪ ኤርትራ ዝምታን መርጣለች። የኤርትራ መንግሥት ሚዲያም ስለ ግጭቱ የጠቀሰው ነገር የለም።

ነገር ግን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው የህወሓትን ድርጊት "ማጉላት" አያስፈልግም በማለት ህዳር 9/ 2013 ዓ.ም በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

"በአስራ አንደኛው ሰዓት የሚጠበቅና ትርጉም በሌለው ድርጊት ማጉላትም ሆነ ምላሽ መስጠት አያስፈልግም" ብለው ያሰፈሩ ሲሆን፤ የትኛውን ድርጊት እንደሆነ በግልፅ አልጠቀሱም።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ሆኑ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ጄኔራሎች የተወሰነው ሠራዊት ከኤርትራ ድንበር በኩል የህወሓትን ኃይል እንደተፋጠጡ አመላክተዋል።

የትግራይ ኃይል የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱን ተከትሎ የተወሰነው የሠራዊቱ አካል ሁለቱን አገራት የሚያዋስናቸውን ድንበር አቋርጠው ወደ ኤርትራ ገብተዋል ተብሏል።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ ውትድርና ኃላፊነት የተመለሱት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌም ከትግራይ ኃይል ጥቃት የተረፉ የሠራዊቱ አባላትን በዛላምበሳ፣ ራማና ሽራሮ መጎብኘታቸውን አስታውቀዋል።

ለሌተናል ጄኔራሉም ሆነ የጠቀሷቸው የሠራዊቱ አባላት የሚገኙባቸው ቦታዎች የኤርትራ ግዛቶችን ተገን ሳያደርጉ መዋጋቱ የማይቻል ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ወታደሮች በበርካታ የኤርትራ ከተሞች የታዩ ሲሆን ቁስለኛ የሠራዊቱ አባላትም በአገሪቱ በሚገኙ ሆስፒታሎች ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ቢቢሲ ትግርኛ ከነዋሪዎችና ከምንጮች ሰምቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በኤርትራ ደቡባዊቷ ከተማ ሰንአፈ በሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል የሠራዊቱ አባላት ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ቢቢሲ ከታማኝ ምንጭ ያገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት

በህወሓትና በኤርትራ አመራር በኩል ያለው ቁርሾ የቀደመ ቢሆንም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ግንኙነታቸውን የቋጨ ሆኗል።

በተለይም በድንበር ግጭቱ ሦስተኛው ዙርና በግንቦት ወር 1992 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሠራዊት የኤርትራን መከላከያ አሸንፎ የደቡብ ምዕራብ በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጥሮ ነበር።

ሽንፈቱ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አሳፋሪ የነበረ ሲሆን በኤርትራውያንም ዘንድ የድንበር ጦርነቱን እያካሄዱ ያሉበት መንገድ ትችትን እንዲያስተናግዱ ምክንያት ሆኗል።

ህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን ከዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ እንድትነጠል የተሳካ ሥራን ሰርቷል። ለረዥም ጊዜያትም ኤርትራ የተገለለች ሆና ቆይታለች።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምንም እንኳን ዓለም አቀፉ የድንበር ኮሚሽን ግዛቶቹን ለኤርትራ ቢወስንም፤ የምዕራባውያን መንግሥታት በድንበር ግጭቱ ላይ ከህወሓት መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወግነዋል በማለት ሲወነጅሉም ነበር።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የምዕራባውያን አጋሮቻቸው እሳቸውንም ከስልጣን ለመገልበጥ "ያሴሩብኛልም" ብለዋል ፕሬዚዳንት ኢሳያስ።

በምላሹም ኤርትራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ታጣቂ ኃይሎች የሆኑትን ግንቦት ሰባት፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴ ነፃነት ግንባር፣ደምሂት መቀመጫ ሆና ነበር። ኢትዮጵያም የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ትደግፍ ነበር።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቀጠናው ላይ አለመረጋጋት በመፍጠርና በሶማሊያ እስላማዊ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ በሚልም የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ ቢጣልባትም ኤርትራ በዚህ ውንጀላ በፍፁም አትስማማም።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አገራቸው ጦርነት ላይ ናት በማለትም ለዲሞክራሲያዊ ለውጦች እምቢተኝነት፣ ተቺዎቻቸውን ለማሰር፣ ነፃ ሚዲያዎችን ለማገድ፣ አስገዳጅ ብሔራዊ አገልግሎትንም በሕዝባቸው ላይ ለመጫን ተጠቅመውበታል።

በተለይም አስገዳጁ ብሔራዊ አገልግሎትንም ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ከአገራቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

የ2010 የሰላም ስምምነት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ካከናወኗቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል በሁለቱ አገራት መካከል እርቅ ማውረድ ነው።

ግንቦት 28/2010 ዓ.ም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበልም ወሰነ። ይህ ውሳኔ አጨቃጫቂ የተባለችውን የባድመ ግዛት ለኤርትራ የሰጠ ነበር።

ለረዥም ዘመናትም ኤርትራ የኮሚሽኑን ውሳኔ ኢትዮጵያ ያለ ቅድመ ሁኔታ ካልተቀበለች ውይይት አይኖርም ስትል ቆይታለች።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔውን ካሳለፈ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰኔ 13/ 2010 ዓ.ም ለሁለቱም አገራት ሕዝብ አስደናቂ ነገር ተፈጠረ።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ "ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ለመረዳትና የወደፊቱንም አቅጣጫ ለመቀየስ" በሚል ልዑካን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ አስታወቁ።

በዚሁም ንግግራቸው ላይ ጠላት ለሚሉት ህወሓት "ጨዋታው አብቅቷ" አሉ።

በወቅቱ ያደረጉት ንግግር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ልታድሰው ባሰበችው ግንኙነት ጠላታቸው ብለው የሚያስቡትና በወቅቱም የኢህአዴግ አካል የነበረው ህወሓትን አለማካተቱ አመላካች ነበር።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከሁለት አስርት ዓመታት ቆይታ በኋላ አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት ከህወሓት መሪ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው ነበር።

ሁለቱ መሪዎች ዛላምበሳ በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በነበረው የዛላምበሳና የሁመራ-ኦምሃጄር ድንበር መከፈትም በነበረው ዝግጅትም እጅ ተጨባብጠዋል።

ከዚያ በፊት ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሐምሌ 1/ 2010 ዓ.ም ወደ አሥመራ መጓዛቸው ዓለምን ያስደመመ ነበር።

ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም እንዲፈጠር በርካታ ጊዜ ቢሸመገሉም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በእምቢተነኝታቸው ፀንተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በኤርትራ መዲና አሥመራም በተቀላጠፈ ትግርኛቸው የሰላም፣ የምጣኔ ሀብት ትብብር መጠንሰሱን በተናገሩበት ወቅት የበርካታ ኤርትራውያንም ልብ ማሸነፍ ችለዋል።

"ባፈረስነው ድልድይና በገነባነው የጥላቻ ግንብ ልጆቻችን እንዲገነቡት ሸክም አንጣልባቸው" ብለዋል።

"ውድ የኤርትራ ሕዝብ ጦርነትም ሆነ የጦርነት ድምፅ ይበቃችኋል። ሰላም ይገባችኋል" በማለትም ተናግረዋል።

ባልተጠበቀ ሁኔታ ለሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠው የነበሩ አገራትን ወደ ሰላም ማምጣታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸነፉ።

ህወትና ህግደፍ

በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር በኋላም ህግደፍ (ህዝባዊ ግንባር ንደሞክራስን ፍትሕን) ደርግን ከማሸነፋቸው በፊት ግንኙነታቸው የተመሳቀለ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 1975 ቁልፍ የሚባሉ የህወሓት መስራቾች በቀድሞው የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር አማካኝነት ኤርትራ ውስጥ ሰልጥነዋል።

በወቅቱ ከነበረው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አመራርም ጋር ወሳኝ በሚባሉ ውጊያዎችም በተለይ በአውሮፓውያኑ 1985 በአንድ ላይ ተሰልፈው ተዋግተዋል።

ሆኖም በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ምክንያት ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ያቋረጡባቸውም ጊዜያት ነበሩ።

ነገር ግን ከ1988 ጀምሮ ሁለቱም አካላት መረዳዳት ጀመሩ፤ በተለይም ህወሓት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት በ1983 ዓ.ም የኤርትራ ተዋጊዎችና ኮማንዶዎች አብረው ነበሩ።

የደርግ ሥርዓትም ከተገረሰሰ በኋላ ለሰባት ዓመታት ያህል ሰላማዊ የሚባል ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርም መስርተው ነበር።

ወጣቶቹ መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወዳጅነታቸው የጠነከረ ቢሆንም እየቆየ ግን መሸርሸር ጀመረ።

ይሄም ቁርሾ ወደ ጦርነት አድጎ በሁለቱ አገራት መካከል ለተከሰተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ሆነ።

ለዚህም ነው ህወሓት ወደ ኤርትራ ጣቷን ብትጠቁም የማያስገርም የሚሆነው።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች