የጎርፍ አደጋ፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ 500 አባወራዎች ተፈናቀሉ

  • 88

የጎርፍ አደጋ፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ 500 አባወራዎች ተፈናቀሉ

በአዋሽ ወንዝ ሙላት የተነሳ 500 አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል

በምዕራብ ሸዋ ዞን በአዋሽ ወንዝ ሞልቶ የነዋሪዎችን መኖሪያ ቤቶችና አካባቢ በማጥለቅለቁ የተነሳ 500 አባዎራዎች መፈናቀላቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ድሪብሳ ዋቁማ ለቢቢሲ ገለፁ።

አስተዳዳሪው አክለውም የጎርፍ አደጋው ከደረሰበት ሰዓት አንስቶ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀው "በዚህም ተሳክቶልናል" ብለዋል።

ጀልባዎችን ከተለያዩ ስፍራዎች በማስመጣት የሰዎችን ህይወት መታደግና ንብረታቸው ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እየሰሩ እንደሆነም ጨምረው አስረድተዋል።

"በዚህ የጎርፍ አደጋ አምስት መቶ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ለእነርሱም የጊዜያዊ መጠለያ አዘጋጅተናል። እንዲሁም የቤት እነስሳቶቻቸው በጎርፉ እንዳይጎዱ የማዳንና ሳር የማቅረብ ስራ እየሰራን እንገኛለን " ብለዋል አስተዳዳሪው።

የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከሚገመተው በላይ ቢሆንም እንኳ፣ ለችግር የተጋለጡትን ማህበረሰቦች እንዲያገግሙ ለማድረግ ከዞኑ አቅም በላይ እንደማይሆን ጨምረው ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመትም የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በምዕራብ ደቡብ ሸዋ ዞን በኢሉ ወረዳ ከ 7900 በላይ ሰዎች ከቀያቸው ማፈናቀሉን አስተዳዳሪው ያስታውሳሉ።

'ለስት ቀንና ሊት በቆጥ ላይ ነው ያሳለፍነው'

በየዓመቱ ክረምት የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰስ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋ ዞኖች የሚገኙ ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጉዳት ያደርሳል።

በዚህ ዓመትም በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀሬ ወረዳ ዲቡ ቀበሌ ወንዙ ሞልቶ በመፍሰሱ የተነሳ፣ ቀበሌው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጉዳት እንደደረሰበት የቀበሌው አስተዳደር አቶ ከበደ ዲሳሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚሁ ቀበሌ በጎርፉ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው በመጠለያ እየኖሩ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ጌጤ ቦርጋ፣ " ዘንድሮ በአገሪቱ ያልነበረ አደጋ ነው የመጣብን" ሲሉ የተፈጠረውን የጎርፍ አደጋ ይገልጹታል።

" ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ነው ደራሽ ውሃው የመጣብን፤ ከሁለት ልጆቼና ከባለቤቴ ጋር ነበርን [ቤት ውስጥ]፤ ባለቤቴ አይነ ስውር ናቸው። ጎረቤት ነው ደርሶ ግድግዳ በመብሳት እንድንቆይበት ቆጥ የሰራልን፤ መያዝ የምንችለውን ይዘን እዚያው ቆጥ ላይ ነው የቆየነው" ይላሉ ወ/ሮዋ።

ላለፉት ሶስት ቀናት የውሃው መጠን መቀነስ ስላልቻለ ሶስት ቀንና ሶስት ለሊት እዚያው ቆጥ ላይ ማሳለፋቸውን ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሶስት ቀን በኋላ ግን ጀልባ ደርሶላቸው ወደ ጊዜያዊ መጠለያ ስፍራ መወሰዳቸውን እና በአሁኑ ሰዓት እዚያ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

" አንድም ነገር ይዘን አልወጣንም፤ ነፍሳችንን ብቻ ይዘን ነው ከቤታችን የወጣነው"

የቀበሌዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቀበሌው ውስጥ የአዋሽ ወንዝ ሙላት ያላጠቃው ቤተሰብ በጣም ጥቂት መሆኑን ገልፀው፣ ከዚህ ቀደም በወንዙ ሙላት የተነሳ የሚደርስ የጎርፍ አደጋ በአካባቢው ብዙ ጊዜ የሚገጥምና የሚታወቅ ቢሆንም የዘንድሮው ግን ከገመቱት በላይ አደገኛ እንደነበር ነዋሪዎቹ ጨምረው ተናግረዋል።

በኦሮሚያ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አባዲር አብዳ የአዋሽ ወንዝ በየዓመቱ በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል የወንዙን ስፋት የመጨመር ፕሮጀክት ተቀርጾ፣ በአምስት ወረዳዎች ውስጥ 52 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዙን ተፋሰስ የማስፋት ስራ ቢሰራም አደጋውን ለማስቀረት አልተቻለም ይላሉ።

ለዚህም ምክንያቱን ሲገልፁ የዘንድሮው የዝናብ መጠን ከመብዛቱ ጋር ተያይዞ ወንዙ ከተሰራለት መከላከያ አልፎ መፍሰሱን ይናገራሉ።

ወንዙ በዘንድሮው ዓመት ከኤጀሬ ውጪ በሌሎች አራት ወረዳዎች ላይም ተመሳሳይ ጉዳት ማድረሱን ኮሚሽነሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስም የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር በማቅረብ ከችግሩ እንዲያገግሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ኮሚሽነር አባዲር ይናገራሉ።

" በአሁኑ ወቅት ከአቅም በላይ የሆነ ነገር አልገጠመንም፤ ጀልባዎች ከተለያዩ ስፍራዎች በማሰባሰብ የማዳን ስራ እየተሰራ ነው፤ ከአቅም በላይ የሆነ ነገር መኖሩ ከተረጋገጠ ደግሞ የሂሊኮፕተር ድጋፍ ለማድረግ ይቻላል" ብለዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች