
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስ] ተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ የተለያዩ የመከላከል እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች። ከእነዚህም መካከል ከባህር ማዶ ለሚመጡ መንገዶኞች ለ14 ቀናት በተዘጋጁ ሆቴሎች ውስጥ በራሳቸው ወጪ እንዲቆዩ መመሪያ አስተላልፋለች።
ይህንንም ተከትሎ በስካይ ላይት ሆቴል ያረፉና ስማቸው እንዳይገለፅ ያልፈለጉ አንድ ግለሰብ ስላሉበት ሁኔታ ለቢቢሲ አጋርተዋል።
ከአውሮፓ በናይሮቢ በኩል አድርገው ከመጡ ጥቂት ቀናት እንዳለፋቸው የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት 1630 ዩሮ እንዲከፍሉ ተጠይቀው መክፈላቸውን ይናገራሉ።
በወቅቱ ከእርሳቸው ጋር የነበሩ መንገደኞችም ሆኑ እርሳቸው ሌሎች ረከስ የሚሉ ሆቴሎች ስለመዘጋጀታቸው እንዳልተነገራቸው የገለፁት ግለሰቧ ስካይ ላይት ሆቴል ውድ መሆኑን ገልጸዋል።
ግለሰቧ እንደሚሉት ምንም እንኳ ቫይረሱን ለመከላከል ከአካላዊ ንክኪ መራቅ አንዱ መንገድ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ቦሌ አየር ማረፊያ በደረሱበት ወቅት በርካታ ሰዎች ተጠጋግተው ይታዩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በሆቴሉ የከፈሉት ምግብን ጨምሮ መሆኑን የሚናገሩት ግለሰቧ ከክፍላቸው መውጣት ስለማይቻል በሆቴሉ ውስጥ ምን ያህል እንግዳ መኖሩን ለማወቅ እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በየዕለቱም የጤና ባለሙያዎች እየመጡ ናሙና እንደሚወስዱ ተናግረው፣ የሆቴሉ አስተዳደር በርካታ ሰው በመኖሩ ሆቴሉ መጨናነቁን እንደነገራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮቪድ-19ን ለመከላከል የኢትዮጵያ ዝግጁነት በሚመለከት በቢቢሲ የተጠየቁት በጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሕክምና አገልግሎቶች ዳይሬክተር ጄነራል የሆኑት አቶ ያዕቆብ ሰማን፤ ሲመልሱ ከባህር ማዶ ለሚመጡ ሰዎች ለለይቶ ማቆያነት እንዲያገለግሉ ተብሎ ስምንት ሆቴሎችና የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተመርጠው መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ ስፍራዎች 5ሺህ ሰው የመያዝ አቅም አላቸው ያሉት አቶ ያዕቆብ፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ማቆያዎቹ እስከ 21 ሺህ ሰዎች የመያዝ አቅም እንዲኖራቸው እንደሚደረግ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የቫይረሱ ምልክትን ለሚያሳዩ እና ቫይርሱ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ እንዳለባቸው ለሚጠረጥሩ ሰዎች ደግሞ የተዘጋጁ 1ሺህ 200 አልጋዎች መኖራቸውን ጨምረው ያስረዳሉ።
