በአማኑዔል ወንድሙ ግድያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምላሽ

  • በአማኑዔል ወንድሙ ግድያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምላሽ - BBC News አማርኛ
  • 182

በአማኑዔል ወንድሙ ግድያ ላይ የኦሮሚያ ክልል ምላሽ

አማኑኤል ወንድሙ

የፎቶው ባለመብት, Kominikeeshinii Bulchiinsa Magaalaa Dambidoolloo

በያዝነው ሳምንት ግንቦት 3፣ 2013 ዓ.ም በቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ አማኑኤል ወንድሙ የተባለ ወጣት በአደባባይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መገደሉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው የመንግሥት ባለስልጣናት ወጣቱ ባለስልጣናትን በመግደል የሚታወቀው 'አባ ቶርቤ' የተባለ የህቡዕ አባል ቡድን ነው በማለት መገደሉን ቢያረጋግጡም ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ሲሉ አስተባብለዋል።

የደምቢ ዶሎ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት በበኩሉ ሰዎችን ሲገድል በነበረው እና 'የአባ ቶርቤ' ቡድን አባል በሆነው ግለሰብ ላይ እርምጃ ተወሰደ ሲልም በፌስቡክ ገጹ ላይ ጽፏል።

የአማኑኤል ወንድሙን ግድያ በተመለከተ ቢቢሲ የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻን የጠየቀ ሲሆን ኃላፊው በክልሉ ህዝብን እያሸበሩ ነው የሚሏቸው አካላት ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።

"በከተሞች ሰውን እየገደሉ ህዝብን ማሸበር የነሱ የእለት ተእለት ተግባር ነው። እነሱ የሚያደርጉት መግደል ነው። ሰላምን ለማስከበር የሚሄደው ኃይል እነዚህ አካላትን አጋልጦ እርምጃ ወስዶ ሊቆጣጠር ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ የተወሰደው እርምጃ የትኛውም አይነት ይሁን ህዝብን አሸብሮ፣ አስፈራርቶ እቆጣጠራለሁ የሚለው ኃይል ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ይህንን በተመለከተም አቅጣጫ ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑንም በተጨማሪ ገልፀዋል።

"ሰው በቤቱ፣ በቀዬው ነው እየተገደለ ያለው፤ በማያውቀው ነገር ነው እየሞተ ያለው፤ እንዲህ አይነት ተግባር በሚፈፅሙ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ እነሱ በሚፈፅሙት ልክ ተመጣጣኝ መሆን አለበት።" በማለትም ይናገራሉ።

ነገር ግን አማኑኤል በአደባባይ ነው የተገደለው ስለሚባለው ጉዳይ ""ወጣቱ የደምቢ ዶሎ ነዋሪ አደባባይ ላይ ነው የተገደለው ስለሚባለው ነገር ግን መረጃ የለኝም" ብለዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን የደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተሰማ ዋሪዮ በበኩላቸው ወጣቱ ቆስሎ ከተያዘ በኋላ ለሕዝብ እንዲታይ ተደረገ እንጂ በአደባባይ አልተገደለም ይላሉ።

"ተጠርጣሪ አይደለም" የሚሉት አቶ ተሰማ፤ ይህ ወጣት ሁለት ሰዎች በጥይት መትቶ እያመለጠ ሳለ በፀጥታ ኃይሎች በጥይት ተመትቶ መያዙን ይናገራሉ።

የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ ወጣቱ በአደባባይ ሲገደል ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"አማኑኤል ሕዝብ የሚወደው ልጅ ነበር" ካሉ በኋላ፤ በጥይት ተመትቶ ከተያዘ በኋላ "ሲገደል በዓይናችን አይተናል" ብለዋል።

እኚህ ነዋሪ እንደሚሉት ከሆነ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ አካላት ወጣቱ ለመያዝ ሲንቀሳቀሱ ወጣቱ ከአንድ ሱቅ እቃ እየገዛ ነበር ይላሉ።

የአማኑኤል ወንድሙ ግድያን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከፍርድ ውጭ የተፈፀመበት ግድያና (extrajudicial killing) በአደባባይ ለህዝብ እንዲታይ የተደረገበት መንገድ እንዳሳሰበው ትናንትና ግንቦት 4/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ማንኛውንም ከፍርድ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎችን የሚያወግዝ መሆኑን አስታውቆ ሁሉም የሕግ አስፈፃሚ አካላት ሕጋዊ መንገዶች ብቻ አንዲተገብሩ መልዕክቱን አስተላልፏል፡

እናንተ ክልሉን እያስተዳደራችሁ እንዴት የወጣቱን የአደባባይ ግድያ አናውቅም ትላላችሁ? ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ የ ክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩላቸው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ወንጅለዋል።

"የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሁልጊዜ የክልሉን ስም ለማጥፋት ስለሚሰራ እነሱ ያላቸው መረጃ እኔ የለኝም። እነሱ ሄደው አይተው ነው ወይስ ከማህበራዊ ሚዲያ ያገኙትን ይዘው ነው ይህንን መግለጫ ያወጡት?" በማለት የሚጠይቁት አቶ ጌታቸው አክለውም

"ይህ መጣራት አለበት። በማስረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ማን ምን አደረገ የሚለውን ነገር ሳይቀበሉ እንዲሁ ሆነ ብሎ ከአንድ ወገን ብቻ መረጃ ይዞ ማውራት ተቀባይነት የለውም። ለሰብዓዊ መብት ነው የምሰራው የሚል ተቋም ጉዳዩን መዘገብ ያለበት በአካል ተገኝቶ ነው። የሚጠየቅም አካል ካለ እርምጃ ሊወሰድ የሚችለው መረጃው ሙሉ ሲሆን ነው።" ይላሉ

ኮሚሽኑ በበኩሉ "ከፍርድ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎች ህዝቦች በሕግ የበላይነት ላይ ዕምነት እንዲያጡ እና በዚህ ረገድ የተገኙ ስኬቶች እንዲቀለበሱ ያደርጋሉ" ከማለት በተጨማሪ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በአፋጣኝ እንዲመረምሩ እና ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጠይቋል።

ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንዳሳሰበው መግለፁ ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ (የአስተዳደራዊ) ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ ተድርጓል ብሎ ነበር።

ከሰሞኑ የወጣው ቪዲዮ ምንን ያሳያል?

በዚህ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወጣቱ ከመገደሉ በፊት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ ይታያል። ቪዲዮን እየቀረጸ የሚገኘው ሰው የወጣቱን ስም እና የትውልድ ስፍራውን ይጠይቀዋል።

እጁ ወደ ኋላ የታሰረው ወጣት አንገቱ ላይ ሽጉጥ ተንጠልጥሎ ይታያል። በወጣቱ እግር ላይ እና በዙሪያው ደም የሚታይ ሲሆን ልብሱም በጭቃ ተለውሷል።

አደባባይ ፊትለፊት የቆመው ወጣት ስሙ አማኑኤል ወንድሙ ከበደ እንደሚባል እና ትውልዱ ደምቢ ዶሎ ከተማ 07 ተብሎ በሚጠራ ስፍራ እንደሆነ ይናገራል።

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎ ተከቦ ይታያል።

የከተማው ኮሚውኒኬሽን ጽ/ቤት እንደሚለው ከሆነ ይህ ወጣት የመንግሥት ባለስልጣናትን በመግደል የሚታወቀው "አባ ቶርቤ' የተሰኘው ህቡዕ ቡድን አባል ነበር።

ወጣቱ ትናንት በቁጥጥር ሥር ከመዋሉ በፊትም ንጋት ላይ ገመቹ መንገሻ የተባለ ግለሰብ በጥይት መትቶ ለማምለጥ ሲሞክር "በጸጥታ ኃይሎች ጠንካራ ትስስር እግሩን ተመትቶ ተይዟል" ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀናት በፊት በደምቢዶሎ ከተማ የኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትዎርክ ጋዜጠኛ የነበረውን ሲሳይ ፊዳ የገደለው የአባ ቶርቤ ቡድን ነው ሲል አክሏል።

አቶ ተሰማ በደምቢዶሎ አካባቢ ከሰሞኑ በኦነግ ሸኔ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ተናግረው፤ ወጣቱ አንገት ላይ የተንጠለጠለው ሽጉጥ ንጹሃን ዜጎችን እና የመንግሥት ኃይሎችን ሲገድልበት የነበረ ነው ብለዋል።

ቢቢሲ የዞኑ ፖሊስ ባልደረቦችን አነጋግሮ ያገኘው ምላሽ አቶ ተሰማ ከሰጡት አስተያየት ጋር ተመሳሳይ ነው።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች