የሴቶችን የወሲብ ቪዲዮ በቴሌግራም ሲሸጥ የነበረው 40 ዓመት ተፈረደበት

  • የሴቶችን የወሲብ ቪዲዮ በቴሌግራም ሲሸጥ የነበረው 40 ዓመት ተፈረደበት - BBC News አማርኛ

የሴቶችን የወሲብ ቪዲዮ በቴሌግራም ሲሸጥ የነበረው 40 ዓመት ተፈረደበት

ደቡብ ኮሪያዊው ቾ ጁ ቢን
የምስሉ መግለጫ,

ደቡብ ኮሪያዊው ቾ ጁ ቢን

የሴቶችን የወሲብ ቪዲዮ በቴሌግራም ቻናል ሲሸጥ የነበረው 40 ዓመት ተፈረደበት

ደቡብ ኮሪያዊው ቾ ጁ ቢን ሴቶችን እያታለለ የወሲብ ቪዲዮ እንዲልኩ በማድረግና በቴሌግራም ቻናል በማሰራጨት ወንጀል ተከሶ 40 ዓመት ተፈርዶበታል።

ይህን የቴሌግራም ቡድን ቾ ጁን ቢን ያስተባብረው እንጂ በርካታ አባላት ያሉትና በድበቅ የሚንቀሳቀስ ነበር ተብሏል።

ቡድኑ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በቴሌግራም ላይ ከሚገኙ ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴቶችን ጭምር በማታለልና በማስፈራራት ቪዲዮ እንዲልኩ ያደርግ ነበር።

ቡድኑ ተንቀሳቃሽ ምሥሎቹን በእጁ ካስገባ በኋላ ለአባላት ብቻ ክፍት በሆኑና 10ሺ አባላት ባሏቸው የቻትሩሞች በመውሰድ ወሲባዊ ቪዲዮዎቹን ለገበያ ያቀርባል።

በዚህ ቻትሩም የሚገኙ አባላት ደግሞ የግለሰቦችን ወሲባዊ ቪዲዮዎቹን ከፍለው ለማየት የተሰባሰቡ ናቸው።

እነዚህ አባላቱ የግለሰቦችን የወሲብ ቪዲዯዎች ለማየት እስከ 1ሺ 200 ዶላር ክፍያ ይፈጽማሉ።

በዚህ ሁኔታ 14 ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴቶችን ጨምሮ 74 ሰዎች የግል ገመናቸው በቪዲዮ ተሰራጭቶባቸዋል።

ቾ ህጻናትን ለወሲባዊ ትርፍ በማዋል ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት 40 ዓመት እስር አከናንቦታል።

ፖሊስ የቾን ማንነት ይፋ ያደረገው ባለፈው መጋቢት ሲሆን ይህ የወሲብ ቪዲዮዎች ነጋዴ ማንነቱ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ 5 ሚሊዮን ደቡብ ኮሪያዊያን ፊርማቸውን አሰባስበዋል።

በመጨረሻም ቾ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ የሆነ የ25 ዓመት ወጣት እንደሆነ ተደርሶበታል።

በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ ተቋማት የቾ የፍርድ ሂደትን በቅርብ ሲከታተሉ ነበር። ምክንያቱም በደቡብ ኮሪያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የበይነ መረብ ወንጀሎችን እንደ ጥፋት ያለመቁጠር አዝማሚያ በመኖሩ ነው።

የቾ የፍርድ ሂደት ለሕዝብ ክፍት እንዲደረግና ጥፋተኛ ሆኖ ከተረጋገጠም ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልበት ጉዳዩን ለሚመለከቱት ፍርድ ቤት 80ሺ የድጋፍ ፊርማዎችና ደብዳቤዎች ደርሰውታል።

አንዳንድ ደብዳቤዎች ቾን ጭራቅ እያሉ ነበር የሚጠሩት።

አቃቢ ሕግ ቾ በእድሜ ልክ እስራት ይቀጣልኝ ቢልም ዳኛው የ40 ዓመት እስር ፍርድ ብቻ አስተላለፍዋል።

የቾ ረዳት የነበሩ ቴሌግራም ቡድን አባላት 15 ዓመትና ከዚያ በታች ተፈርዶባቸዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች