ደቡብ ኮሪያ የላላ ብሎን ታዋቂው የጂምናስቲክ ተወዳዳሪ ወደ አገሯ እንዲገባ ረድቶታል አለች

  • ደቡብ ኮሪያ የላላ ብሎን ታዋቂው የጂምናስቲክ ተወዳዳሪ ወደ አገሯ እንዲገባ ረድቶታል አለች - BBC News አማርኛ

ደቡብ ኮሪያ የላላ ብሎን ታዋቂው የጂምናስቲክ ተወዳዳሪ ወደ አገሯ እንዲገባ ረድቶታል አለች

የደቡብ ኮሪያ ወታደሮች

ደቡብና ሰሜን ኮሪያ ድንበር ላይ ያለው አጥር ብሎን መላላቱ በርካታ ሰሜን ኮሪያውያን ሳይታዩ ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዲያመልጡ እየረዳቸው እንደሆነ ደቡብ ኮሪያ አስታውቃለች።

በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ በድንበር አጥር በኩል ዘሎ ከሰሜን ወደ ደቡብ ኮሪያ የተሻገረ ሰው አግኝተው መያዛቸውን ባለስልጣናት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ይሄው ግለሰብ የቀድሞ የሰሜን ኮሪያ የጅምናስቲክ ተወዳዳሪ ነበር።

የደቡቡ ኮሪያ መከላከያ ኃይልም ሁለቱን አገራት በሚያዋስነው ድንበር ላይ የሚገኘው ግንብ ለመቆጣጠሪያ የተገጠመው መሳሪያ ላይም ፍተሻ እንደሚያደርግና ማስተካከያዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የድንበር መቆጣጠሪያው በአውሮፓውያኑ 2015 ላይ የተገጠመ ሲሆን ሰዎች በድንበሩ አካባቢ ሲጠጉ ለጥበቃ ሰራተኞች መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።

የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ዛሬ ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት በግንቡ ላይ የነበረ አንድ ብሎን በመላላቱ ምክንያት የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው መሳሪያ በአግባቡ እየሰራ አልነበረም።

ሰሜን ኮሪያዊው የቀድሞ የጂምናስቲክ ተወዳዳሪም በዚህ ምክንያት አልፎ ከገባ በኋላ ነበር በጥበቃ ካሜራዎች የታየው።

በሰሜን ኮሪያ በድብር በኩል አድርገው ተሻግረው ወደ ደቡቡ ኮሪያ የሚገቡ ሰዎች ጉዳይ በአገሪቱ ትልቅ መነጋገሪያ ሲሆን መንግስት ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ አይደለም ብለው የሚተቹ በርካቶች ናቸው።

እንደ ደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ ባለስልጣናት የጂምናስቲክ ተወዳዳሪው ዘልሎ መግባቱን ለማረጋገጥ አጥሩን በድጋሚ እንዲዘለውና እንዲያሳያቸው አድርጓል ሲሉ ዘግበዋል።

በየዓመቱ 1 ሺ ሰዎች ከሰሜን ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚመጡ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሰብአዊ መብት ጥሰትና አፈናን ሸሽተን ነው የምንመጣው ይላሉ።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች