የማንዴላ የልጅ ልጅ በፖሊስ ጥቃት ተሰነዘረብኝ አለ

  • የማንዴላ የልጅ ልጅ በፖሊስ ጥቃት ተሰነዘረብኝ አለ - BBC News አማርኛ

የማንዴላ የልጅ ልጅ በፖሊስ ጥቃት ተሰነዘረብኝ አለ

የማንዴላ የልጅ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Mayibuye Melisizwe Mandela facebook

የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ ፖሊስ "ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት አድርሶብኛል" በሚል ክስ እንደሚመሰርት የመገናኛ ብዙሃን ዘገቡ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ያደጉበትን የመቀሄኬዝዌኒን ቅርስ ከሌሎች ሦስት ሰዎች ጋር ጎብኝተው በሌሊት ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ፖሊሱ አስቁሟቸው እንደደበደቧቸው ማይቡዬ ማንዴላ ተናግሯል፡፡

ክስተቱ የተፈጸፈመው ግንቦት 8 ነው ተብሏል፡፡

ፖሊሶቹ ጭንቅላቱ ላይ መምታትን ጨምሮ "የጭካኔ" ድርጊቶች እንደፈጸሙባቸው ተናግሯል። በዚህም ከግራ ዓይኑ በላይ መሰንጠቁን ገልጿል፡፡

ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት ፖሊስ ተሳፍረውበት የነበሩትን መኪና ለመፈተሽ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግሯል፡፡

"መሬት ላይ እንድንተኛ መጠየቅ ሲጀምሩ ፈቃደኛ ባለመሆን መኪናውን ተደግፌ ቆሜ እንድፈተሽ ጠየቅኩኝ። ይህን ያልኩት በዋነኝነት ዝናብ ስለነበረና እና በጠጠር መንገድ ላይ ስለሆንን ነበር" ሲል ለአይኦኤል የዜና አውታር አስረድቷል፡፡

ማይቡዬ ማንዴላ ከደረሰባቸው ጥቃት በኋላ በፌስቡክ ገጹ ፎቶዎቹን አጋርቷል፡፡

በምስራቅ ኬፕ አውራጃ ለሚገኘው ማዲይራ ፖሊስ መምሪያም ስሞታውን አስገብቷል፡፡

መምሪያው ምንም አስተያየት ሳይሰጥ ጉዳዩን አውቀዋለሁ ማለቱም ተዘግቧል፡፡• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች