የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ኦባማ ትራምፕን የመረጡ የሂስፓኒክ ማኅበረሰብ አባላትን ወቀሱ

  • የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ኦባማ ትራምፕን የመረጡ የሂስፓኒክ ማኅበረሰብ አባላትን ወቀሱ - BBC News አማርኛ

የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ኦባማ ትራምፕን የመረጡ የሂስፓኒክ ማኅበረሰብ አባላትን ወቀሱ

ኦባማ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ድምጻቸውን ለዶናልድ ትራምፕ የሰጡ የሂስፓኒክ ዝርያ ያለቸው አሜሪካውያን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በንግግራቸው በተደጋጋሚ የሚሰጡትን 'ዘረኛ' አስተያየት ችላ ብላችኋል በማለት ወቀሱ።

ኦባማ ሲናገሩ ዶናልድ ትራምፕ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር በተያያዘ ያላቸውን አቋም የሚደግፉት እነዚህ ሰዎች ፕሬዝዳንቱ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አመለካከት ዘንግተዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

በተጨማሪም ድምጻቸውን ለዶናልድ ትራምፕ የሰጡና በአንድ ወቅት በማቆያዎች የነበሩ ያልተመዘገቡ ስደተኞችንም ወቅሰዋል።

በምርጫው ውጤት መሰረት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2016 በተካሄደው ምርጫ ካገኙት ድምጽ በበለጠ በዘንድሮው ብዙ ድምጽ ከሂስፓኒክ ማኅበረሰብ ማግኘት ችለዋል።

በ2016 ከሂስፓኒክ ማኅበረሰብ 28 በመቶ የሚሆኑት ዶናልድ ትራምፕን መርጠው የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ምርጫ ግን ይህ ቁጥር ከፍ ብሎ 32 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ተመዝግቧል።

'ዘ ብሬክፋስክ ክለብ' ከሚባለው የረቡዕ ቃለ መጠይቅ ዝግጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት ባራክ ኦባማ ''በርካታ ሂስፓኒኮች ድምጻቸውን ለዶናልድ ትራምፕ በመስጠቻቸው ብዙ ሰዎች ተደንቀዋል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

''ነገር ግን በርካታ ኢቫንጀሊካል ሂስፓኒኮች ትራምፕ ስለ ሜክሲኮ ተወላጆች የሚናገረውን አስተያየት ያውቃሉ፤ ያልተመዘገቡ ስደተኞችን እንዴት እንደሚያስተናግድ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ድምጻቸውን ሰጥተውታል'' ብለዋል።

ኦባማ በዝግጅቱ ላይ የቀረቡት በቅርብ ያስመረቁት መጽሐፋቸውን ለማስተዋወቅ ነበር። መጽሐፉ 'ኤ ፕሮሚስድ ላንድ' ይባላል፤ ወይም በግርድፉ 'ስፋይቱ ምድር' እንደማለት ነው።

ይሄው የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ መጽሐፍ እስካሁን በሰሜን አሜሪካ ብቻ 1.7 ሚሊየን ቅጂዎች ተሽጧል።

የሪፐብሊካን ፓርቲው ፍራንክ ሉንትዝ ደግሞ የኦባማን ንግግር ተከትሎ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ''የማይረባ ትንተና ነው" በማለት ያጣጣሉት ሲሆን ሌሎችም ትችቱን ተቃውመውታል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች