ኮሮናቫይረስ፡ የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ

  • ኮሮናቫይረስ፡ የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ - BBC News አማርኛ

ኮሮናቫይረስ፡ የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ሕይወታቸው አለፈ

የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አል ማህዲ

የሱዳን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አል ማህዲ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሦስት ሳምንታት ያህል በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሆስፒታል ገብተው ሕክምና ሲደረግላቸው እንደነበር ቤተሰቦቻቸውና ብሔራዊው ኡማ ፓርቲያቸው ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

እዚያው ሕክምና ሲከታተሉ በነበሩበት ነው ሐሙስ ዕለት ሕይወታቸው ያለፈው።

ማህዲ ሆስፒታል የገቡት በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የአል ማህዲ 21 የቤተሰብ አባላት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነበር።

የ84 ዓመቱ ማህዲ በአውሮፓውያኑ 1989 በቀድሞው የአገሪቷ ፕሬዚደንት ኦማር ኣል በሽር በተመራ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ሲወገዱ የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጨረሻው ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።

እርሳቸው ይመሩት የነበረው ኡማ ፓርቲም በፕሬዚደንት አልበሽር አስተዳዳር ሥር ከነበሩ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ ነበር።

ማህዲ ምንም እንኳን አልበሽር ባለፈው ዓመት በተነሳ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ቢወገዱም በአገሪቷ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

ሕልፈታቸውን ተከትሎም አገሪቷን እያስተዳደረ ያለውና በሲቪልና ወታደራዊ የሥልጣን ከፍፍል የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሦስት ቀናት የሃዘን ቀን ማወጁን ሮይተርስ ዘግቧል።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ በሱዳን እስካሁን 16 ሺህ 052 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 1 ሺህ 197 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች