የኢንስታግራም ገጿን ለማስተዋወቅ ተማሪ የመሰለችው ግለሰብ ክስ ተመሰረተባት

  • የኢንስታግራም ገጿን ለማስተዋወቅ ተማሪ የመሰለችው ግለሰብ ክስ ተመሰረተባት - BBC News አማርኛ

የኢንስታግራም ገጿን ለማስተዋወቅ ተማሪ የመሰለችው ግለሰብ ክስ ተመሰረተባት

ኦድሪ ኒኮል

የፎቶው ባለመብት, Handout via CBS

ተማሪ በመምሰል ፍሎሪዳ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት የገባችው የ 28 ዓመት ሴት በቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

ፖሊስ እንደሚለው ኦድሪ ኒኮል ፍራንሲኮኒ ሰኞ ዕለት ማያሚ ወደሚገኘው የአሜሪካ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት የኢንስታግራም ገጿን የሚያስተዋውቀውን በራሪ ወረቀቶችን መስጠት ጀመረች፡፡

ፍራንሲስኮኒ ተማሪ ለመምሰል ቦርሳ አንግታ እና ስኬትቦርድ [ባለጎማ በእግር የሚገፋ ተሽከርካሪ ነው] ይዛ ነበር ተብሏል፡፡

በስርቆት፣ በትምህርት ተቋም ጣልቃ በመግባት እና የፖሊስ መኮንንን ውሳኔ በመቃወም ተከሳለች፡፡

ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን ጥፋተኛ አይደለሁም ብላ ተከራክራለች፡፡

አቃቤ ህጎች እንዳሉት ከሆነ ፍራንሲስኮኒ ማህበራዊ ሚድያዋን የሚያስተዋውቅ ወረቀት ለማሰራጨት ሰኞ ማለዳ ላይ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ተገኝታለች፡፡

አጠራጣሪ ባህሪዋ በትምህርት ቤቱ የጸጥታ ኃላፊዎች እይታ ውስጥ ቢከታትም በኋላም ሳትቆም ቦታውን ለቃ ወጥታለች፡፡

ፖሊሶች ያስተዋወቀችውን የኢንስታግራም ገጿን በመጠቀም ተከታትለው ይዘዋታል፡፡

አንድ ተማሪ ጉዳዩን "እብደት ነው ፡፡ በጣም አስፈሪ ነው" ሲል ይገልጻል።

ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው ፍራንሲስኮኒ እአአ በ 2017 ሥራዋን ያጣች የቀድሞ የፖሊስ መኮንን ናት፡፡

አንድ የማያሚ-ዴድ ካውንቲ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ቃል አቀባይ ለጋዜጣው ድርጊቱን "አሳዛኝ" ሲሉ ገልጸው በአካባቢው የተሟላ የፀጥታ ግምገማ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች