ትግራይ፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የዘመቻው የመጨረሻ ምዕራፍ መጀመሩን አስታወቁ

  • ትግራይ፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የዘመቻው የመጨረሻ ምዕራፍ መጀመሩን አስታወቁ - BBC News አማርኛ

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡትን የሦስት ቀናት የጊዜ እንደማይቀበሉ አሳውቀው ነበር።

"ሕግ የማስከበሩ ዘመቻችን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መከላከያ ሠራዊት የመጨረሻውን እና ሦስተኛውን የዘመቻ ምዕራፍ እንዲፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቶታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንሰትሩ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፉት የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች ሰላም ወርዶ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ እየወተወቱ ባሉበት ወቅት ነው።

የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር በደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የተላኩ ሦስት የቀድሞ የአፍሪካ አገራት ፕሬዝደንቶችም ዛሬ ጠዋት በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ከቀናት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአፍሪካ መሪዎች ካለ አክብሮት የመነጨ ይህን ልዑክ ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ አስታውሰው፤ "ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግን እንደ ሕጋዊ አካል ቆጥሮ የሚደረግ ውይይት አይኖርም" ብለዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በመግለጫቸው "የወዳጆቻችን ስጋት እና ምክረ ሃሳብ ከግምት እያስገባን፤ በውሳጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግን ጥረትን አንቀበልም። ስለዚህም ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ተቀባይነት ከሌላው እና ሕጋዊ ካልሆነ ጣልቃ ገብነት እንዲቆጠብ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ጣልቃ-አለመግባት መሠረታዊ ምርሆዎችን እንዲያከብር በአክብሮት እናሳስባለን" ብለው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛሬው መግለጫቸው፤ "በዚህ ዘመቻችን ለንጹሐን ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ በሕዝባችን ላብ የተሠራችው የመቀለ ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳያገኛት የሚቻለው ሁሉ ይደረጋል" ብለዋል።

መንግሥት 72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ የሰጠው ለሁለት ዓላማ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ "በአንድ በኩል ዋና ፍላጎቱ ሕግ ማስከበር እንጂ ጦርነት አለመሆኑን መግለጥ ነው። . . . ሁለተኛው ደግሞ የህወሓት የጥፋት ዓላማ ዘግይቶም ቢሆን የገባው አንድም ሰው ከተገኘ፤ ያንንነ ሰው ለማትረፍ እንዲቻል ነው" ያሉ ሲሆን፤ በተሰጠው የጊዜ ገደብ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ሚሊሻ እና ልዩ ኃይል አባላት እጃቸውን እየሰጡ ገብተዋል ብለዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ወታደራዊ ግጭት አምርቶ ከሦስት ሳማንት በላይ ሆኗል።

ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የመንግሥት ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ አቅራቢያ መድረሳቸውም ተገልጿል።

በመቀለ ከተማ ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል የተባለውን ወታደራዊ ግጭት በማስመልከት ዓለም አቀፍ ተቋማትና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በከተማዋ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ከ500 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሉባት ከመተማ መሆኗ የሚነገር ሲሆን ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በነበሩት ባለፉት ሦስት ሳምንታት የነዳጅና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች እጥረት በከተማዋ መከሰቱ ሲነገር ነበር።

የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ከመቀለ ከተማ ቀደም ብሎ የክልሉ ትላልቅ ከተሞች የሆኑትን ሽረ፣ አክሱም፣ አድዋና አዲግራትን መቆጣጠሩን ባለፈው ሳምንት ማሳወቁ ይታወሳል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች