ጃዋር መሐመድ ፡ ጋዜጠኛ ያሲን ጁማና አምስት የጃዋር ጠባቂዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

  • 47

ጃዋር መሐመድ ፡ ጋዜጠኛ ያሲን ጁማና አምስት የጃዋር ጠባቂዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

ያሲን ጁማ

በአቶ ጃዋር መዝገብ ከተከሰሱ ሰዎች መካከል አምስቱ እንዲሁም ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል መባሉን ጠበቆቻቸው ለቢቢሲ አረጋገጡ።

በአቶ ጃዋር መዝገብ ለተከሰሱ 14 ሰዎች ጠበቃ ከሆኑት መካከል አንዱ ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) ለቢቢሲ የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂ የነበሩት አምስት ሰዎች ዛሬ በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ አለመቅረባቸውን ገልፀው ለዚህም ዐቃቤ ህግ የሰጠው ምክንያት በኮቪድ-19 መያዛቸውን መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም በተጨማሪ ኬንያዊው ጋዜጠኛ የያሲን ጁማ ጠበቆች ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ከድር ቡሎ እንዲሁ ፖሊስ ጋዜጠኛው በኮሮናቫይረስ ተይዞ በለይቶ ማቆያ እንደሚገኝ ለችሎት ማስረዳቱንና ጋዜጠኛውም በነበረው የችሎት ቀጠሮ ላይ አለመገኘቱን አረጋግጠዋል።

ቶኩማ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደገለፁት በአቶ ጃዋር መሐመድ ጉዳይ ላይ ዛሬ ቀጠሮ መኖሩን የሰሙት ድንገት አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ መሆኑን እና አራት ጠበቆች ፍርድ ቤት በተገኙበትም ወቅት ዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ቀጠሮ አስይዞ ቀርቦ እንደነበር ይናገራሉ።

በወቅቱ በመዝገቡ ከተከሰሱ 14 ተጠርጣሪዎች መካከል ዘጠኝ ብቻ መቅረባቸውን የሚናገሩት ቶኩማ ዳባ (ዶ/ር) ጌቱ ተረፈ፣ በሽር ሁሴን፣ ሰቦቃ ኦልቀባ፣ ኬኔ እና ዳዊት ሆርዶፋ አልተገኙም ብለዋል።

ያልተገኙበትን ምክንያት አቃቤ ሕግ ሲጠየቅ በኮቪድ-19 መያዛቸው ገልፆ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን ማስረዳቱን ጠበቃው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ዐቃቤ ሕግ መረጃውን ያገኘው ወደ 7፡30 ላይ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን በመናገር ዛሬ ሦስት ምስክሮች በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ለመመስከር ተዘጋጅተው እንደነበር ጨምሮ ማስረዳቱን ገልፀዋል።

አምስቱ ተጠርጣሪዎች ስላልቀረቡና ምስክሮቹን በዚህ ምክንያት ማሰማት ስለማልችል ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሎ መጠየቁን አስረድተዋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በኮቪድ-19 የተያዙት እነዚህ ግለሰቦች የጃዋር መሐመድ ጠባቂ የነበሩ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት እለት ጀምሮ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች በተለየ ቤተሰቦቻቸውን እንዲያገኙ እንደማይፈቀድላቸው አመልክተዋል።

በተጫመሪም ምግብ እንደማይገባላቸው፣ ለአንድ ወር ያለ ቅያሪ ልብስ መቆየታቸውን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ማቅረባቸውን በሽታውም የያዛቸው እስር ቤት ውስጥ እያሉ በመሆኑ አያያዛቸው ላይ ጉድለት እንዳለ ማሳያ ነው በማለት መከራከራቸውን ይናገራሉ።

በተጨማሪም እነዚህ እስረኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ከዐቃቤ ሕግ ከመስማት ውጪ ያየነው ማስረጃ ባለመኖሩ ለፍርድ ቤቱም ለእኛም ማስረጃ ይቅረብልን በማለት መከራከራቸውን ጠበቃው ቶኩማ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አክለውም ከደንበኞቻቸው ጋር ተቀራርቦ በመመካከር ለምስክሮች መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ እንዲችሉ ሁሉም የኮቪድ-19 ተመርምረው ውጤታቸው እንዲቀርብ፣ በቫይረሱ መያዛቸው የተገለጹት አምስት ሰዎች ማስረጃ እንዲቀርብ አቤቱታ ማቅረባቸውን ይገልጸዋል።

ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር አድምጦ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል የተባሉ ማስረጃ ይቅረብ፣ ሌሎቹ ምርመራ ተደርጎ ውጤታቸው ይቅረብ፣ ስለአያያዛቸውም የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቀርቦ እንዲያስረዳ ብይን ሰጥቶ ምስክር ለመስማት ለነሐሴ 11/2012 ዓ.ም ሰኞ ቀጠሮ መስጠቱ ተናግረዋል።

ለኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማም ለነሐሴ ደግሞ በቀጣይ ቀን ነሐሴ 12/2020 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱን ጠበቃው አረጋግጠዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች