ኮሮናቫይረስ፡ ስለኮቪድ-19 እስካሁን ያላወቅናቸው 9 ነገሮች ምንድን ናቸው?

  • 29 ማርች 2020
  • 390
የመድሃኒት ቅመማን የሚያሳይ ምስልImage copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የመድሃኒት ቅመማን የሚያሳይ ምስል

የኮሮናቫይረስ በፊትም የነበረ ቢሆንም ዓለም ግን በደንብ የተገነዘበው ከባለፈው ታኅሳስ ወር ጀምሮ ነው።

ስለቫይረሱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በመላው ዓለም ሳይንቲስቶች የሚያደርጉት ብርቱ ጥረት ቢኖርም ብዙ የማናውቃቸው ነገሮች ግን አሁንም አሉ።

አሁን በመላው ዓለም የዚህን አወዛጋቢ ቫይረስ ስውር ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ሁላችንም የቤተ ሙከራ አካል ሆነናል። ምክንያቱም ቫይረሱ በምድራችን በመሰራጨት ሁላችንም ተጋላጭ የመሆናችን እድል ሰፍቷልና።

የኮሮናቫይረስ ሲነሳ የሚከተሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ የሚሹ ናቸው።

1. ምንል ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል?

ይህ በጣም መሰረታዊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ጥያቄም ነው። በእርግጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠርና በምርመራ የተረጋገጡ የታማሚዎች ቁጥር መኖሩ የታወቀ ነው። ይህ ግን ቫይረሱ ከያዛቸው ሰዎች ብዛት አንጻር በጣም ትንሽ ቁጥር ነው።

ቁጥሩ በራሱ ትክክል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ምክንያቱም ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውም ምንም የህመም ምልክት ሳይታይባቸው እንደ ጤነኛ መንቀሳቀስ ይችላሉና።

ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በፍጥነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መሳሪያ ቢሰራ ለተመራማሪዎች ነገሩ ቀላል ይሆናል። ከዚያ በኋላ ነው ቫይረሱ በፍጥነት መሰራጨቱም ሆነ መገታቱ ሊታወቅ የሚችለው።

2. ኮሮናቫይረስ ምንል ገዳይ ነው?

በአጠቃላይ የቫይረሱ ታማሚዎች ቁጥር እስካልታወቀ ድረስ የቫይረሱን የገዳይነት ደረጃ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡት ሰዎች መካከል 1 በመቶ አካባቢ የሚሆኑት ብቻ ሞተዋል።

ነገር ግን በጣም በርካታ በሽታው ኖሮባቸው ምልክቱ ግን የማይታይባቸው ሰዎች ካሉ የሞት መጠኑ ከዚህም ያነሰ ነው ለማለት ይቻላል። ስለዚህ ትክክለኛ አሃዙን ወይም የገዳይነቱን ደረጃ ለማስቀመጥ ትክክለኛው የታማሚዎች ቁጥር መታወቅ አለበት ማለት ነው።

3. የቫይረሱ ምልክቶ ምን ምን ናቸው?

ዋነኞቹ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። እነዚህን በጥንቃቄ መከታተል ያስፈልጋል።

የመተንፈሻ አካላት መድረቅን ተከትሎ የራስ ምታት የሚያስከትል ሲሆን በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ ደግሞ ተቅማጥም አሳይቷል። በሌላ በኩል አንዳንዶቹን ታማሚዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ የማሽተት አቅማቸውን ያጠፋዋል የሚሉም አሉ።

ዋናው ጥያቄ ግን በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ የጉንፋን ምልክት የሚመስሉ በአፍንጫ ፈሳሽ የማመንቸትና የማስነጠስ ምልክቶች መኖራቸው ነው። ዋናዎቹ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዚህ ሳቢያ ሰዎች መታመማቸውን ሳያውቁ በበሽታው ሊጠቁ ይችላሉ።

ኮሮና
Banner

4. በሽታውን በማሰራጨት ሕጻናት የሚኖራቸው ሚና ምንድን ነው?

ህጻናት በትክክል በበሽታው ይያዛሉ። ነገር ግን ከሌሎች የዕድሜ ክልል ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ህጻናት የሚታይባቸው የበሽታው ምልክት በጣም አናሳና የመሞት እድላቸውም ዝቅ ያለ ነው። ከዚህ አንጻር ህጻናት ዋነኛ የበሽታው አስተላለፊዎች ናቸው።

ምክንያቱም አንደኛ የበሽታው ምልክት በብዛት አይታይባቸውም፤ ሁለተኛው ደግሞ ህጻናት ብዛት ካላቸው ሰዎች ጋር ይገናኛሉ፣ ይተቃቀፋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህሉ ስርጭት በህጻናት አማካይነት እንደሆነ ለማወቅ የተደረገ ጥርት ያለ የጥናት ውጤት የለም።

5. ቫይረሱ በትክክል የት ነው የመጣው?

ቫይረሱ በፈረንጆቹ 2019 መጨረሻ አካባቢ ከቻይና ዉሃን ከተማ ውስጥ ከሚገኝ የእንስሳት ገበያ አካባቢ ካላ ቦታ እንደሆነ ይነገራል። ሳርስ-ኮቭ-2 ተብሎ የሚጠራው ኮሮናቫይረስ የሌሊት ወፍን ከሚያጠቃው ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት አለው።

በመሆኑም ቫይረሱ ከሌሊት ወፍ ወደ ሌላ እንስሳ፤ ከዚያም ወደ ሰው ተሸጋግሯል የሚል ሰፊ ግምት አለ። በዚህ ሂደት ግን አስቸጋሪውና ፈጣን መልስ የሚሻው ጥያቄ በሰው እና በሌሊት ወፍ መካከል ቫይረሱን የሚያሸጋግረው እንስሳ ማን ነው የሚለው ነው?

ይህ ጥያቄ ካልተመለሰ በመላው ዓለም ያለው የቫይረሱ ስርጭት በቁጥጥር ስር ቢውል እንኳ በዚህ ማንነቱ ባልታወቀው እንስሳ አማካኝነት ቫይረሱ ድጋሚ መከሰቱ የማይቀር ነው ማለት ነው።

6. ቫይረሱ በበጋ ወራት ስረጭቱ ሊቀንስ ይችላልን?

ጉንፋንና ኢንፍሉዌንዛ ከበጋ ይልቅ በክረምት በብዛት ይከሰታሉ፤ ነገር ግን ኮሮናቫይረስን ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ስርጭቱን ሊገታው እንደሚችል ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የሳይንስ አማካሪዎች ቫይረሱ በአየር ሁኔታ መለዋወጥ ስርጭቱ ስለመቀነሱም ሆነ ስለመጨመሩ የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።

በአጠቃላይ ግን በበጋ ወራት በሽታው ስርጭቱ ከፍተኛ ከሆነ በክረምት የባሰ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በክረምት የተለመዱ በሽታዎች ሆስፒታሎችን ከማጨናነቃቸው ጋር ተዳምሮ ደግሞ ችግሩን ያገዝፈዋል።

7. አንዳንድ ሰዎች ለምን በጣም የጠና ምልክቶችን ያሳያሉ?

ኮቪድ-19 ለብዙዎቹ ሰዎች ቀላል በሽታ ነው። ነገር ግን 20 በመቶ የሚሆኑት በሽታው ይጠናባቸዋል። ለምን?

የሰዎች በሽታ የመከላከል አቅም ከበሽታው አይነት ጋር የሚኖረው ሁኔታ አንዱ ምክንያት ሲሆን የዝርያ ሁኔታም ግምት ውስጥ ሊገባ ይችላል።

እነዚህን ምክንያቶች በሚገባ መረዳት ሰዎች የሚያስፈልጋችውን እንክብካቤ ለማድረግ ይጠቅማቸዋል።

8. በሽታው ምን ያክል ጊዜ ሊቆይ ይችላል? በድጋሚ ልንያዝ እንችላለን?

ብዙ የሚባሉ ነገሮች ቢኖሩም በግልጽ ቫይረሱ ምን ያህል ጊዜ ሊያጠቃን እንደሚችል የሚገልጹ በጥናት የተደገፉ መረጃዎች ውስን ናቸው።

ቫይረሱን ለማሸነፍ ታማሚዎች በቂ በሽታውን የመከላከያ አቅም ሊያዳብሩ ግድ ይላቸዋል። ነገር ግን በሽታው ከተከሰተ ገና ጥቂት ወራትን ብቻ ያስቆጠረ በመሆኑ ሰፊ የመረጃና ትንተና ለመስጠት ጊዜው እራሱ አጭር ነው።

ለሁለተኛ ጊዜ የተጠቁ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ማረጋገጥ ከባድ እንደሆነና በአብዛኛው ነጻ እንደሚባሉም ይነገራል።

በሽታው ምን ያህል ጊዜ ሊያሰቃይ እንደሚችል ማወቁ ወደፊት ለቫይረሱ የሚደረጉ ህክምናዎችንና ጥንቃቄዎችን ለማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም ለጊዜው ግን የተረጋገጠ መረጃ የለም።

9. ቫይረሱ ቅርጹን ሊቀይር ይችላልን?

ቫይረሶች ሁልጊዜ ቅርጻቸውን ይቀይራሉ፤ በዋናነት ከዝርያ መለያቸው አንጻር ሲታይ ግን ምንም የተለየ ለውጥ አይኖረውም።

እንደ አጠቃላይ ቫይረሶች ረዘም ላለ ጊዜ በቆዩ ቁጥር ገዳይነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል የሚል ጥቅል እውቀት አለ፤ ይህ ግን ለኮሮናቫይረስ ዋስትና ሊሆን አይችልም።

አሁን ትልቁ አሳሳቢ ነገር ቫይረሱ ቅርጹን የሚቀያይር ከሆነ አንድና ተመሳሳይ የበሽታ ተከላካይ ክትባትን ለማበልጸግ ፈታኝ ይሆናል። ልክ ኢንፍሉዌንዛ ላይ ተሞክሮ እንዳልተሳካው ሁሉ ኮሮናቫይረስ ላይም ላይሆን ይችላል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች