ትግራይ፡ በመቀለ 'ሕገወጥ ሰልፍ ሊያካሂዱ ነበር' የተባሉ 9 ወጣቶች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

  • 52

ትግራይ፡ በመቀለ 'ሕገወጥ ሰልፍ ሊያካሂዱ ነበር' የተባሉ 9 ወጣቶች ላይ ክስ ሊመሰረት ነው

የመቀለ ከተማ ቀዳማይ ወያነ ፍርድ ቤት

በመቀለ 'ሕገወጥ ሰልፍ ሊያካሂዱ ሲሉ ተይዘዋል' የተባሉ ዘጠኝ ወጣቶች ላይ ከሰባት ቀን በኋላ ክስ ሊመሰረት ነው።

ወጣቶቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጀምሮ የትግራይ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መቆየቱን ትናንት [ሐሙስ] ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ምርመራውን በመጨረሱ ፋይላቸውን ክስ እንዲመሰረት ወደ ዐቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው እየታየ የሚገኝበት የመቀለ ከተማ ቀዳማይ ወያነ ፍርድ ቤትም ዘጠኙን ወጣቶች እስር ቤት እንዲቆዩ አዟል።

በትግራይ "የክልሉን መንግሥት ለመጣል የሚያነሳሳ መፈክር ይዛችሁ ተገኝታችኋል" በሚል በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚህ ዘጠኝ ወጣቶች ትናንት ለሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ታውቋል።

ወጣቶቹ ከ46 ቀናት በፊት፣ ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በመቀለ የሮማነት አደባባይ ላይ መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚያነሳሳ መፈክር ይዘው መገኘታቸውን እንዲሁም ያልተፈቀደ ሠልፍ ለማካሄድ ሲወጡ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ገልጾ ነበር።

በወቅቱ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም ፖሊስ በተደጋጋሚ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ በመጠየቅ ከ46 ቀናት በላይ በእስር ላይ ቆይተዋል።

ወጣቶቹ ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት ችሎቱን ማንም እንዲታደም ያልተፈቀደ ሲሆን ቢቢሲ ከችሎቱ በኋላ የሚመለከታቸውን በማናገር መረዳት እንደቻለው ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ በመጨረስ ጉዳያቸውን ለዐቃቤ ሕግ አስረክቧል። በዚህም ከሰባት ቀናት በኋላ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ታውቋል።

ወጣቶቹ 'ፈንቅል' ከተባለው እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት እንደሌላለቸው መናገራቸውንና ቡድኑም ይህንኑ ማረጋገጡን ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

ዘጠኙ ወጣቶች በሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ ላይ የክልሉን መንግሥት በመቃወም ሕገወጥ የተቃወሞ ሰልፍ ሊያካሂዱ ነበር በሚል በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ቆይተዋል።• ተጨማሪ ትኩስ ዜናዎች